Benefits of Treating Cholesterol

Cholestrol

Cholesterol

ኮሌስትሮል

የደም ቅባት መጠን መዛባት (Dyslipidemia) የሚባለው ህመም የደም ውስጥ የኮሌስትሮል ወይም ስብ መጠን ከተለመደው ውጭ ሲዛባ የሚከሰት ነው። ይህ ሁኔታ የልብና የደም ሥር በሽታዎች ተጋላጭነትን ይጨምራል። ተላላፊ ያልሆነ ይህ ህመም፣ ቅባቶች በደም ስር ቧንቧዎች ውስጥ በመከማቸት እንዲዝጉና እንዲደፈኑ በማድረግ ወደ ልብ፣ አንጎል እንዲሁም ወደ ሁሉም የሰውነት ክፍላችን የሚሄድ የደም ፍሰትን ይገድባል።

የደም ቅባት መዛባት (Dyslipidemia) ዋና ዋና አይነቶች

የደም ቅባት መጠን መዛባት በሶስት ዋና ዋና የህመም አይነቶች ይከፈላል። እነዚህም፡-

  • የኮሌስትሮል መብዛት (High Cholesterol): በተለይ “ጎጂ ኮሌስትሮል” (LDL) ሲበዛ
  • የደም የስብ መጠን መብዛት (High Triglycerides):
  • የጥሩ ኮሌስትሮል መጠን ማነስ (Low HDL):

“ጥሩ” እና “ጎጂ” ኮሌስትሮል ምንድን ናቸው?

  • HDL (ጥሩ ኮሌስትሮል): የ HDL ዋና ስራ ኮሌስትሮልን በሰውነት ውስጥ ከሚገኙ ሕብረ ሕዋሳት ወደ ጉበት ማዛወር ነው። ይህ በሰውነት ውስጥ ስብን ለማከፋፈል ይረዳል እና የልብ ችግርን አደጋን ይቀንሳል።
  • VLDL/LDL (ጎጂ ኮሌስትሮል): VLDL ኮሌስትሮል በጉበት ተዘጋጅቶ ወደ ደም ውስጥ ይለቀቃል። የVLDL ቅንጣቶች በዋነኛነት ትራይግሊሰርይድ የተባለውን የስብ አይነት ወደ ሰውነታችን (ቲሹ) ያጓጉዛሉ። VLDL ከ LDL ኮሌስትሮል ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ LDL በዋነኝነት ኮሌስትሮልን ወደ ቲሹዎች ያጓጉዛል (ይህም ለደም ስር መዘጋት አስተዋጽኦ ያደርጋል)።

በኢትዮጵያ ያለው ስርጭት

በኢትዮጵያም ያሉ የዳሰሳ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የኮሌስትሮል ህመም ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነውን የማህበረሰብ ክፍል እያጠቃ እንደሆነ የጤና ሚኒስቴር እ.ኤ.አ በ2015 ባደረገው አገር አቀፍ ጥናት አረጋግጧል (Gebreyes et al. PLoS ONE. 2015)።

የኮሌስትሮል ህመም ክብደት፣ የአመጋገብ ዘይቤ፣ ማህበራዊ ሁኔታ፣ የሃብት መጠን፣ ሃይማኖት፣ ዘር፣ እድሜና ጾታ ሳይለይ በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል።

ምርመራ እና መደበኛ መጠን

የሊፒድ ፕሮፋይል (Lipid Profile) የተባለው የደም ምርመራ ስለ አንድ ሰው የልብና የደም ሥር (cardiovascular) ጤንነት ጠቃሚ መረጃ ይሰጣል።

የተለመደው (Normal) የኮሌስትሮል መጠን

  • ከ 20-39 ዕድሜ፡
    • አጠቃላይ ኮሌስትሮል < 200 mg/dL
    • LDL ኮሌስትሮል < 100 mg/dL
    • HDL ኮሌስትሮል > 40 mg/dL
    • Triglycerides < 150 mg/dL
  • ከ 40-59 ዕድሜ፡
    • ጠቅላላ ኮሌስትሮል < 200 mg/dL
    • LDL ኮሌስትሮል < 70 mg/dL (የልብ ህመም ወይም የስኳር ህመም ካለ)
    • HDL ኮሌስትሮል > 40 mg/dL
    • Triglycerides < 150 mg/dL
  • ከ 60 በላይ ዕድሜ፡
    • ጠቅላላ ኮሌስትሮል < 200 mg/dL
    • LDL ኮሌስትሮል < 70 mg/dL (የልብ ህመም ወይም የስኳር ህመም ካለ)
    • HDL ኮሌስትሮል > 40 mg/dL
    • Triglycerides < 150 mg/dL

ማሳሰቢያ: እነዚህ አጠቃላይ መመሪያዎች ብቻ መሆናቸውን ልብ ሊባል ይገባል። ለልብ በሽታ በሚያጋልጡ ሌሎች ሁኔታዎች ላይ በመመስረት የእርስዎ የግል ኮሌስትሮል ኢላማዎች ሊለያዩ ይችላሉ።

የኮሌስትሮል መብዛት ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ከፍተኛ ኮሌስትሮል መጠን ለብዙ ሰዎች ምንም ዓይነት ምልክት አያሳይም (ምልክት አልባ ነው)። ከፍተኛ ኮሌስትሮል በሰውነትዎ ውስጥ ሌሎች ችግሮችን እስኪያመጣ ድረስ ምንም ዓይነት ምልክቶች ላያዩ ይችላሉ።

ከፍተኛ ኮሌስትሮል እንዳለ ለማወቅ ብቸኛው መንገድ የደም ምርመራ በማድረግ ነው!

ኮሌስትሮልን እንዴት ዝቅ ማድረግ ይቻላል?

የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች መደበኛ የኮሌስትሮል መጠንን ወደነበሩበት ለመመለስ ይረዳሉ።

  • የአካል ብቃት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር
  • የእግር ጉዞ ማድረግ
  • ከሁሉም በላይ ደግሞ የኮሌስትሮል መጠንን የሚቀንሱ ምግቦችን መመገብ። (ለምሳሌ፡- አጃ፣ አቮካዶ፣ እና ኦሜጋ 3 የያዙ እንደ አሳ ያሉ ምግቦች)

ኮሌስትሮልን የማከም ዋነኛ ጥቅሞች

ኮሌስትሮል በመድሃኒትም ሆነ ያለመድሃኒት (በአኗኗር ለውጥ) እንዲቀንስ የሚመከረው ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ከባድ የጤና እክሎች ለመከላከል ነው።

1. ድንገተኛ የልብ ድካም (Heart Attack) መከላከል

ይህ የደም ስር መጥበብ ልብ ላይ ሲከሰት የደረት ህመም ያመጣል። በተለይም እንቅስቃሴ በምናደርግበት ጊዜ ልባችን ደም ማዳረስ ስለሚያቅተው ሰቅዞ የሚይዝ የደረት ህመም ያስከትላል። ይህ ህመም ወደ ክንድ፣ አንገት፣ ሆድ ወይም ጀርባ ሊሰራጭ ይችላል። የልብ ጡንቻ የደም ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ ሲገደብ ድንገተኛ የልብ ድካም (Heart attack) የሚባል ገዳይ አደጋ ይደርሳል።

2. ስትሮክን (Stroke) መከላከል

ወደ አንጎላችን የሚሄደው የደም ስር ሲጎዳ ደግሞ ድንገተኛ የአንጎል መታወክ (ስትሮክ) ይባላል። ለአንጎል የሚሄደው የደም አቅርቦት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ሲስተጓጎል የሚከሰት ነው። ይህም እንደ ደረጃው ሙሉ ሰውነትን ፓራላይዝ ከማድረግ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል።

3. ፔሪፌራል አርተሪያል ዲዚዝ እና ጋንግሪን (Gangrene) መከላከል

ወደ እግር የሚሄደው የደም ፍሰት ሲቋረጥ (Peripheral Arterial Disease) ደግሞ ጋንግሪን (Gangrene) ያመጣል። በደቂቃዎች ውስጥ የተዘጋው ደም በህክምና ወይም በኦፕሬሽን እንዲስተካከል ካልተደረገ፣ ይህ ሁኔታ እስከ እግር ወይም እጅ መቆረጥ ሊያደርስ ይችላል።

ሕክምና እና ክትትል በላንድማርክ ሆስፒታል

በላንድማርክ አጠቃላይ ሆስፒታል የተሟላ የኮሌስትሮል ህክምናና ክትትል በውስጥ ደዌና የልብ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪሞቻችን ማግኘት ይችላሉ።

ለበለጠ መረጃና ቀጠሮ ይደውሉልን፡

  • 📞 0115-52-57-19
  • 📞 0115-52-57-61

አድራሻችን:

📍 ከሜክሲኮ ወደ ቄራ በሚወስደው መንገድ ከገነት ሆቴል ከፍ ብሎ ያገኙናል።

Google Map

በሶሻል ሚዲያ ይከተሉን:

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *